ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የኖርዌይ የውጭ እና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያዩ

Norway and Ethiopiaየኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ዛሬ መስከረም 5 ቀን 2011 ዓም የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አኒከን ሁይትፈልድት እና ልኡካቸውን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ ወገኖች በሁለትዮሽ፣ በቀጠናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት አንደገለጹት ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ ረጅም ዘመናትን የስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳቸው ገልጸው ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሰራ ነው ብለዋል። በኖርዌ የልማት ትብብር አማካኝነት ኖርዌ በኢትዮጵያ በማህበራዊና በኢኮኖሚው ዘርፍ እያደረገች ያለውን ጉልህ እንቅስቃሴ በተለመለከተ ክቡር ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን አጠቃላይ ሪፎርም በተመለከተ ገለጻ በማደረግ ኖርዌ ለሪፎርሙ መሳካት ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥልም ክቡር ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲመሰረት እየተጫወተች ያለውን ሚና በተመለከተም ክቡር ሚኒስትሩ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል። ኢትዮጵያ እና ኖርዌ በዓለም አቀፍ መድረኮች በአየር ንብረት ለውጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጠንካራ ግንኙነት እንደላቸውና በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ክቡር ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አኒከን ሁይትፈልድት በበኩላቸው በኢትዮጵያ እተካሄደ ያለውን አጠቃላይ ሪፎርም ኖርዌ እንደምታደንቅ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለሴቶች እኩልነት በሰጠችው ትኩረት በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን እንደተገነዘቡም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት እምነታቸው መሆኑንም አብራርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በቀጠናው እየተጫወተች ያለውን አጠቃላይ አንቅስቃሴም አድንቀዋል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮችም ጉልህ ሚና የምትጫወት አገር መሆኗን በማንሳት በዚህ በኩል ከኖርዌ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንድምትቀጥል እምነታቸው መሆኑንም የተከበሩ አኒከን ሁይትፈልድት በንግግርቸው አንስተዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖንን ለመቋቋም ኢትዮጵያ በደን ተከላ እያደረገች ያለውን ከፍተኛ አንቅስቃሴም አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ ጉብኝት በማደረግ ላይ የሚገኘው የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኖርዌይ ፓርላማ ውስጥ መቀመጫ ካላቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ ሲሆን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፓርላማ የውጭ እና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመወያየት የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ።

ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱት በ1939 ዓም ሲሆን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ስቶክሆልም በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ከኖርዌ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ በመቀጠል ላይ ትገኛለች። በተመሳሳይ ኖርዌይ በ1984 ዓም በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን በመክፈት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግኑኝነት አጠናክራ በማስቀጠል ላይ ትገኛለች።