በስዊድን ከሚኖሩ ኢትዮዽያውያ እና ትውልደ ኢትዮዽያውያን ጋር የውይይት መድረክ እ.ኤ.አ April 13, 2019 ተካሄደ

2.4የኢትዮዽያ ኤምባሲ በስውዲን ከሚገኙ ኮሚኒቲዎች ጋር በመተባበር በሀገሪቱ ከሚኖሩ በርካታና ሁሉንም ኢትዮዽያውያን እና ትውልደ ኢትዮዽያውያን ያሳተፈ የጋራ የውይይት መድረክ April 13, 2019 በስቶክሆልም ከተማ አካሂዷል፡፡
የውይይት መድረኩም በሀይማኖት አባቶች ቃለ ቡራኬ የተጀመረ ሲሆን በማሰቀጠል በስዊድንና በሌሎች የኖርዲክ አገራት የኢትዮዽያ መንግስት ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የሆኑት ክቡር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በአገራችን አጠቃላይ የለውጥ ሥራዎች ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ክቡር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በሚያራምዱት የመደመር፣ የፍቅር፣ የይቅርታና የእርቅ የአስተምሮ ፍልስፍና አማካኝነት አገራችን ኢትዮጵያ በለዉጥ ምህዋር ዉስጥ መንቀሳቀስ ከጀመረች እነሆ ድፍን አንድ ዓመት ተቆጠረ። በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ዉስጥ በርካታ አመርቂ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድሎች መመዝገባቸውን ። ከተመዘገቡት በርካታ ድሎች ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል የአገሪቱን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር በሚል በስራ ላይ እንዲዉል ተደርጎ የነበረዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ መደረጉ፣ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የነበሩ በርካታ ወገኖቻችን ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉ፣በሽብርተኝነት ተፈርጀዉ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ፍረጃዉ እንዲነሳላቸዉ መደረጉ እና በአጠቃላይ በዉጭ አገር ሆነዉ በትጥቅ የታገዘ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩና እንዲሁም ያለትጥቅም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሚዲያ ተቋማት እና ወትዋቾች/አክቲቪስቶች/ ወደ አገራቸዉ ገብተዉ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ማካሄድ የሚያስችሏቸዉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸዉ፣ በአብዛኛዉ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ የገቱና ለዴሞክራሲ ምህዳር መጣበብና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸም ምክንያት የነበሩት የጸረ ሽብር አዋጅ፣የበጎ አድራጎት አና ማህበራት አዋጅ እና የመረጃ ነጻነትና የሚዲያ አዋጅ እንዲሻሻሉ በማድረግ የዴሞክራሲ ምህዳሩ እስካሁን በአገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንዲሰፋና ሰብዓዊ መብቶች ያለገደብ የሚከበሩበት ስርዓት ለመዘርጋት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በመደረግ መሆኑን ገልፀዋል ።

5
በአገራችን የሚካሄደዉ ቀጣዩ ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና በመራጮች ዘንድ ተቀባይነት ያለዉ እንዲሆን ለማድረግ የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እና የተቋም አቅም ግንባታ ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል።በአገራችን ለማካሄድ የታሰበዉን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚመራዉና የሚያስተዳድረዉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከየትኛዉም የፖለቲካ አካል ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ሁሉንም በእኩልነት ማስተናገድ እንዲችል የሚያደርጉት በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸዉ፣ በኢኮኖሚ መስክ ማክሮ ኢኮኖሚን የተረጋጋ ለማድረግ፣የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እንዲሁም የአገሪቱን ከፍተኛ የዕዳ ጫና ለመቀነስ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ተካሂዷል በመካሄድ ላይም ይገኛል።ከዚህ ጎን ለጎን በኢኮኖሚዉ ዉስጥ የግል ዘርፉን ሚና ለማጠናከር ፣የዉጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የአገራችንን ኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረዉ ለማድረግ ፣ለዜጎቻችን የስራ ዕድል የሚፈጠርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በርካታ የህግ ማዕቀፍና የአሰራር ማሻሻያ ጥናቶች እየተካሄዱና በተግባር ላይ እየዋሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በዲፕሎማሲዉ መስከ የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል።ከዚህ አኳያ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለዉ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ላለፉት 20 ዓመታት የዘለቀዉ ሰላምም ሆነ ጦርነት የሌለበት ወይም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ አገላለጽ ሞት አልባ ጦርነት ዉጥረት ተወግዶ በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም ስምምነት መደረሱና ተቋርጦ የነበረዉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደገና መጀመር መቻሉ ነዉ።ከዚህ ጎን ለጎን ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት እና ወዳጅነት በማጠናከር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ዉህደት እንዲፈጠር ለማድረግ አገራችን ግንባር ቀደም ሆና እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።ከባህረ ሰላጤዉ አገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት በማሻሻል ትርጉም ያለዉ የኢኮኖሚ ግንኙነትና የጋራ መተማመን የሚያጠናክሩ ስራዎች ተከናዉነዋል።አገራችን በኢጋድ፣በአፍሪካ ህብረት ፣በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በሌሎች ባለብዙ ወገን መድረኮች ያላትን ተሳትፎ በማጠናከር የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ተግባር በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

2.2
በመጨረሻም ክቡር አምባሳደር በየጊዜዉ በሚያጋጥሙ ችግሮች እና እንቅፋቶች ሳንበገርና ችግሮችንና እያስወገድን ለሌሎች ተጨማሪ ድሎች መብቃት ይኖርብናል ብለዋል። ከዚህ አኳያ ከስሜትና ከጭፍን ጥላቻ ተላቀን የተረጋጋና ምክንያታዊነት የተለበሰ አቋምና አመለካከት ላይ መድረስና አርአያ ሆኖ መገኘት ያስፈልገናል። ስለሆነም የዚህ የዛሬዉ ስብሰባችን ዋና ዓላማም የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ለመወያየትና ብዥታዎችን ለማጥራት እንዲሁም በአገራችን የተጀመረዉን ለዉጥ ለማስቀጠልና አስተማማኝ ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግና የአገራችን ኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረዉና ለዜጎቻችን ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር እንዲቻል በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንና ትዉልድ ኢትዮጵያዉያን በሚኖራቸዉ ሚና ላይ የጋራ መግባባት ለመድረስ እንዲያስችለን ይህን መሰል መድረክ ለወደፊቱም በየጊዜዉ ከተለያዩ ኮሚዩኒቲ አመራሮች ጋር በመተባባር የምናመቻች ሲሆን እየተነጋገርንና እየተወያየን በሄድን ቁጥር ይበልጥ እንደምንግባባና በጋራ ለመስራት እንደምንችል እምነቴ የጸና ነዉ ብለዋል።

8
በስብሰባውም በኤምባሲው ዲፕሎማት በአገራችን አጠቃላይ ወቅታዊ ጉዳዮች እና ዳያስፖራው ለአገሩ ድጋፉን አጠናክሮ በሚቀጥልበት ጉዳዮች ዙሪያ ገለፃ ቀርቧል፡፡ ከቀረበው ገለፃ እና አጠቃላይ የአገራችን የለውጥ ሂደት አስመልክቶ ከዳያስፖራው ጠቃሚ ጥያቄዎች እና አሰተያየቶች ቀርበው ውይይት ተካሂዷባቸዋል፡፡
በመጨረሻም በስውዲን የሚኖሩ የኢትዮዽያ ኮሚውኒቲ የአገራችንን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ከኤምባሲው ጋር በመስራት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በውይይቱ ማጠቃላይ ላይ ባቀረቡት የጋራ አቋም አሳውቀዋል፡፡