12ኛው የኢትዮዽያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል በስቶክሆልም ተከበረ

612ኛው የኢትዮዽያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ከ200 በላይ የሚሆኑ ኢትዮዽያውያንና ትውልደ ኢትዮዽያውያን በተገኙበት እ.ኤ.አ ዲሴምበር 9 ቀን 2017 በደማቅ ሁኔታ በስቶክሆልም ከተማ “በሕገ መንግስታችን የደመቀ ህብረ ብሄራዊነታችን ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡

በዓሉም ለትግሉ ሰማእታት የ 1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማካሄድ የተጀመረ ሲሆን፣ በመቀጠልም በስዊድንና በሌሎች የኖርዲክ አገራት የኢትዮዽያ መንግስት ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የሆኑት ክቡር አምባሳደር ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በዓሉን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም የዘንድሮው የአገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን “በሕገ መንግስታችን የደመቀ ህብረ ብሄራዊነታችን ለህዳሴያችንʼʼ በሚል መሪ ቃል በአገር ቤትና በውጭ አገራት በሚገኙ ሚሲዮኖቻችን በመከበር ላይ ይገኛል:: በዓሉ በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በዓል መላው የኢትዮዽያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረውላቸው እና በሀገራቸው የህዳሴ ጉዞ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆናቸውን ያስመሰከሩበት እንዲሁም በቀጣይ ተከባብረውና ተቻችለው በጋራ አብሮ መኖር እንዲችሉ ዋስትና የሆናቸውን ሕገ-መንግሥት ያፀደቁበት ታሪካዊ እለት ለማስታወስ ነው ብለዋል፡፡

1

ክቡር አምባሳደሩም አክለው እንደገለጹት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት አጠቃላይ መነሻ በአገራችን ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታችንን ማፋጠን፣ በአገራችን የሚገኙ ሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን በመጠቀም በነፃ ፍላጎታቸውና ፈቃዳቸው በአገራቸው ዋስትና ያለው ዴሞክራሲን ማስፈን እና የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ እንዲሁም አንድ የጋራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ መገንባት ነው፡፡ በመሆኑም ሕገ-መንግሥታችን በአገራችን ቀደም ሲል በነበሩት ሥርዓቶች ሰፍኖ የነበረውን የተዛባ የሕዝቦች ግንኙነት በማስተካከል አዲስ የኢትዮጵያዊነት ማንነትና ሕብረ ዝምድና ላይ በመመስረት በሕዝቦች መካከል እኩልነትና መከባበር እንዲኖር እና የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ፖለቲካዊ አንድነት፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ማህበራዊ ትስስር እንዲጠናከር መሰረት ጥሏል።

አገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶች የሚገኙባት አገር እንደመሆኗ መጠን ያለው ብዝሃነት ሊበታትነን የሚችል አደጋ ሳይሆን የጥንካሬ ምንጭ እንደሆነ በመገንዘብ አገራችን ከነበረችበት የማያባራ ጦርነት፣ ድህነትና ኋላቀርነት የሚያወጣ፣ ለብሄርና ለሃይማኖት ጥያቄዎች ተገቢና ትክክለኛ መፍትሄዎች የሚሰጥ ፌዴራላዊ ስርዓት እና ይህንኑ ብዝሃነት መሰረት ያደረገ ህገ-መንግስት በመጽደቁና ተግባራዊ እየተደረገ በመሆኑ በአገራችን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ሊከፈት ችሏል፡፡

በዚህም ሕገ-መንግሥታችን የየራሳቸው አኩሪ ባሕልና መልክአ ምድር እና አሰፋፈር ያላቸው ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በተለያዩ የግንኙነት መስኮች ተሳስረው አብረው የሚኖሩባት የጋራ ጥቅማቸውን፣ መብታቸውን እና ነፃነታቸውን በጋራ እና በተደጋጋፊነት የሚያራምዱበት፣ በከፍተኛ መስዋእትነት የተገኘውን ዲሞክራሲና ሰላም ዘላቂነት ያረጋገጡበት ሰነድ ነው፡፡ ስለሆነም በዛሬው እለት 12ኛውን የብሔሮቸ ብሔረሰቦች በዓል ስናከብር እነዚህን እሴቶች የበለጠ ለማጎልበት እና አገራችን፣ የጀመረችውን የሕዳሴ ጉዞ እውን ለማድረግ ቃል መግባት ይኖርብናል፡፡ በአገራችን ብዝሃነትን ማስተናገድ በሚያስችልና የህዝባችን የረጅም ጊዜ የራስ ማስተዳደር ጥያቄን ምላሽ የሰጠ የፌዴራላዊ ስርዓት ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረ ከ20 ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰቡ በሁሉም ህብረተሰባችን ዘንድ በሚፈለገው ደረጃ ግንዛቤ ባለመያዙ የተመዘገቡ ውጤቶችን በየጊዜው የሚፈታተኑ ችግሮች ሲያጋጥሙን ቆይቷል፡፡ በቅርቡም በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ከወሰን ማስከበርና ማንነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች፣ ለወጣቶች በቂ የስራ እድል ያለመፍጠር፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሚፈለገው ደረጃ ያለመፍታት፣ የህዝቡን ፍትሃዊ የሆነ ጥያቄ በጥቂት ጽንፈኛ ሃይሎች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ተወስዶ ሁከትና ግጭቶች ተከስቷል፤ በዚህም የበርካታ ወጣቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም የፀጥታ አስከባሪዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ የህዝብ ንብረት ላይም ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፡፡ መንግስት በየወቅቱ የእነዚህ ሁከቶችና ግጭቶች ዋነኛ ምክንያቶች እየለየ እና እርምጃ እየወሰደ ያለ ቢሆንም አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብቶች የሚፈታተኑ ችግሮች እየተከሰቱ ነው።

በአገራችን ቀደም ሲልም ተመሳሳይ ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች አስከፊና ለበርካታ ዜጎች መፈናቀል፣ ህይወት መጥፋትና ንብረት ጉዳት ምክንያት ሆኗል፡፡ መንግስት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በዜጎች ላይ ኢ-ሰብኣዊ ድርጊት የፈጸሙ አካላትን መለየትና እርምጃ ለመውሰድ ብርቱ ክትትል እያደረገ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴም በርካታ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

መንግስት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ህገ መንግስቱን የማስከበርና የዜጎች የሰብኣዊ መብት ጥሰት እንዳይከሰት ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ በሌላ በኩል በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ይበልጥ እንዲጎለብት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ለአብነትም የአገሪቱ የምርጫ ህግ ማሻሻል፣ የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተዘዋዋሪ ፈንድ መመደብ፣ ከማንነት ጋር በተያያዘ ከህዝቡ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በየክልሉ በጥልቀት የመታደስና ብቁ አመራሮችን ወደ መንግስት ኃላፊነት እንዲመጡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም መንግስት የበለጠ ብቃትና ቅንነት ያላቸው ግለሰቦች ወደ ሃላፊነት እንዲመጡ ለማድረግ የጀመራቸው የሪፎረም ሥራዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ክቡር አምባሳደሩም በመጨረሻ ንግግራቸው ክህዳር 29 በአገራችን ታሪክ ብዝሃነትን በማስተናገድ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግስታዊ ዋስትና የተረጋገጠበት ዕለት በመሆኑ በዓሉን በጋራ ማክበር በአዲስቷ ኢትዮጵያ ዕኩልነት፣ መቻቻል፣ መከባበርና በመፈቃቀድ መርህ ላይ የተመሠረተውን ዲሞክራሲያዊ አንድነታችንን ለማጠናከር፣ የጋራ እሴቶቻችንን ይበልጥ ለማዳበርና የአገራችን መልካም ገፅታ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በእስካሁኑ ስኬታማ ጉዟችን ያጋጠሙንን ችግሮች በጋራ እየፈታን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ፣ በህዝቦች የጋራ ጥረት የገነባናትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ይበልጥ ደምቃ እንድትታይ ቃላችንን የምናድስበት ሊሆን ይገባል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

9

በማስከተልም የኢትዮዽያ ኮሚኒቲ እና ማህበራት ተወካዮች የእንኳን አደረሳችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡ በመልእክታቸው ዜጎች ህገ መንግስቱ የሰጣቸውን መብት በማስጠበቅ የአብሮነታችንን ባህል መጐልበት ያለበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “ሕብረ-ብሔራዊነትና ዴሞክራሲ” በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይትም ተካሂዷል፡፡ በዝግጅቱም ፍፃሜ የተለያዩ የብሄር ብሄረሰቦች ሙዚቃ በመጫወት በዓሉ ተጠናቋል፡፡2 3 5 7 8