ፊንላድ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ተጠየቀ

Ethiopia-Finlandየኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከፊንላንድ ፕሬዝዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ ጋር ባደረጉት ውይይት በርካታ ኢትዮጵያዊያን በኢንጅነሪንግ እና አርክቴክቸር ዘርፎች በፊንላንድ መማራቸውን ጠቁመው ይኸው ተጠናክሮ ኢንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለራሷ ሰላም አልፋ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እየሰራች ነው ያሉት ዶ/ር ወርቅነህ የሶማሊያ መንግስት የጸጥታ መዋቅሩን ለማሻሻል እንዲሁም የደቡብ ሱዳንን የሰላም ሂደት ለመደገፍ ለሚደረገው ጥረት እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር ወርቅነህ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይን የጉብኝት ግብዣ ለፕሬዝዳን ሳውሊ ኒኒስቶ አቅርበውላቸዋል፡፡

ክቡር ፕሬዝዳንቱም ጉብኝቱ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እንደሚያጠናክር አምናለሁ በማለት የጉብኝቱን ግብዣ በደስታ መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡

በየትኛውም ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር እንቆማለን በአገሪቱ የተካሄደውን የፖለቲካ ማሻሻያም እንከታተላለን እንደግፋለንም ብለዋል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡

በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ሰላም ጉዳይ ላይም ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ዶ/ር ወርቅነህ ከፊንላንድ አቻቸው ቲሞ ሶይኒ እንዲሁም የአገሪቱ ፓርላማ የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚህም ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የፓለቲካ ምህዳር ማስፋት በተመለከተ ክቡር ሚኒስትሩ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡